አልበርት አንስታይንን ወደ ህይወት ተመልሶ ከሰዎች ጋር እንዲነጋገር ተደረገ

ከወደ ጥንቆላው ዓለም በሙት መንፈስ አማካኝነት ከብዙ ዓመታት በፊት ያለፉ ቤተሰብ እና ሌሎች ወዳጆችን ማዋራት እንደሚቻል ሲነገር ብዙዎቻችን ሰምተን ይሆናል፡፡ ታድያ በእንግሊዙ የድምፅ ሰሪ ኩባንያ ኤፍሎሪዝሚክ እና በኒውዚላንዱ የዲጁታል ሰብ አበልፃጊ አኒኪው ወስጥ ያሉ አጥኚዎችም ታሪካዊውን የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይንን በድምፅም በምስልም መስሎ የሚናገር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓትን ይዘው መጥተዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ተጠቃሚዎች ልክ እራሱ አልበርት አንስታይንን እንደሚያዋሩት በሚመስላቸው መልኩ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁት አልመው ነው ይህን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት በትብብር የገነቡት፡፡ ኩባንያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ስመ ጥሩን ሳይንቲስት ለዚህ ስራ የመረጡት በሰዎች ዘንድ ባለው የባለ ምጡቅ አዕምሮ ባለቤትነት እይታ፣ ታሪካዊ ስብዕና፣ የቴክኖሎጂ ልክፍተኝነቱ እንዲሁም ብዙዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊያቀርቡለት የሚፈልጉት ሰው ነው ብለው በማመናቸው ነው፡፡

ምስለ አንስታይን ሊቅነቱን እንዲያስመሰክርና በተቻለ መጠንም እውነተኛ ይመስል ዘንድ የረቀቁ ኮምፒውተራዊ ስልቶችን አኒኪው ሰጥቶታል፡፡ ሆኖም የአልበርት አንስታይንን ድምፅ በትክክል በማስመሰሉ ረገድ ነገሮች ፍፁም አልሆኑም፡፡ አጥኚዎቹ ማግኘት የቻሏቸው የሳይንቲስቱ ታሪካዊ ንግግሮች የሚያመላክቱት አልበርት አንስታይን እንግሊዝኛው ከፍተኛ የጀርመንኛ ተፅዕንዖ ያለበት፣ ሲናገርም በዝግታ፣ ትህትና፣ ጠቢብነት እንዲሁም ሞቅ ባለ ቶን ተሞልቶ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም አልበርት በሚናገረው እንግሊዝኛና የድሮ መቅርፀ ድምፆች ባላቸው የጥራት መጓደል ሳብያ ተመራማሪው ትክክለኛው ድምፁ ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን ለመለየት አስቸግሯቸው ነበር፡፡

ታድያ ብዙዎቹ ተጠቃሚዎች በቴክኖሎጂው አማካኝነት ከአንስታይን ጋር ሲገናኙ ስለ ድምፁ ትክክለኝነት ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው አምነዋል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባትም አጥኚዎቹ ከዚህ ስመጥር የፊዚክስ ተመራማሪ ጋር አንድ አይነት ያልሆነ፤ ግን ደግሞ በሚያነጋግሩት ተጠቃሚዎች ዘንድ ሊቀር የሚችል ሌላ ድምፅ ለምስለ አንስታይኑ ሰጥተውታል፡፡ ይህ አዲስ ድምፅ ምስለ አልበርት አንስታይን የተወሰነ ጀርመንኛ ዘዬ ባለው መልኩ እንዲናገርና ለተጠቃሚዎችም ንግግሩ የተጫዋችና በወዳጅ ቅርበት የተዋዛ መስሎ እንዲታያቸው የተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም አጥኚዎቹ ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት ምስለ አልበርት ተጠቃሚዎችን ሲያነጋግር ልክ ከራሱ ዕውቀት ተነስቶ የሚናገር ሊቅ እንዲመስል ጭምር አድርገውታል፡፡

ከድምፁ ባሻገርም ይህ የአልበርት ዲጂታል ምስለእኔን ሲሰሩት ልክ እንደ ደንበኞች አገልግሎት ጥሪ ወይም የግል ረዳት ሁሉ የተጠቃሚዎችን ጥያቄ በፍጥነት እንዲመልስ አድርገው መስራት ነበረባቸው፡፡ አጥኚዎቹ ይህን ለማሳካት ሰው ሰራሽ አስተውሎቱን ከረቀቀ ኮምፒውተራዊ አሰራር ያቀናጁት ሲሆን ማሻሻያዎቹን ማድረግ ከጀመሩበት ከሁለት ሳምንታት በኋላም ስርዓቱ ለጠያቂዎቹ ምላሽ ለመስጠት የሚወስድበትን ጊዜ ከ12 ሴኮንድ ወደ 3 ሴኮንድ ማውረድ ችለዋል፡፡

ታድያ ተመራማሪዎቹ ይህ የአልበርት አንስታይን ዲጂታል ምስለእኔ በሰው ልጆች እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት መካከል ሊደረግ ስለሚችለው መስተጋብር የመጀመሪያ እርምጃ አድርገው ተመልክተውታል፡፡

እርስዎም ይህን ሊንክ በመጠቀም አልበርት አንስታይንን ሊያዋሩት ይችላሉ https://einstein.digitalhumans.com/

ምንጭ፤ ቴክኖሎጅ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲቱት Tech Xplore ጠቅሶ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *